ኦሪት ዘጸአት Orit ZeTseAt
Exodus / Shemot #27
In Amharic and English

Can’t see Amharic font?

 

ኦሪት ዘጸአት 27

Exodus 27

1 ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ መሠዊያ ከግራር እንጨት አድርግ አራት ማዕዘንም ይሁን ከፍታውም ሦስት ክንድ ይሁን።

1 And thou shalt make an altar of shittim wood, five cubits long, and five cubits broad; the altar shall be foursquare: and the height thereof shall be three cubits.

2 በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን ታደርጋለህ፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ይሁኑ በናስም ለብጠው።

2 And thou shalt make the horns of it upon the four corners thereof: his horns shall be of the same: and thou shalt overlay it with brass.

3 አመድ የሚሆንባቸውን ምንቸቶች፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አድርግ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አድርግ።

3 And thou shalt make his pans to receive his ashes, and his shovels, and his basons, and his fleshhooks, and his firepans: all the vessels thereof thou shalt make of brass.

4 እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የናስ መከታ አድርግለት ለመከታውም አራት የናስ ቀለበት በአራት ማዕዘኑ አድርግለት።

4 And thou shalt make for it a grate of network of brass; and upon the net shalt thou make four brasen rings in the four corners thereof.

5 መከታውም እስከ መሠዊያው እኵሌታ ይደርስ ዘንድ በመሰዊያው በሚዞረው በእርከኑ ታች አድርገው።

5 And thou shalt put it under the compass of the altar beneath, that the net may be even to the midst of the altar.

6 ለመሠዊያውም ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሠርተህ በናስ ለብጣቸው።

6 And thou shalt make staves for the altar, staves of shittim wood, and overlay them with brass.

7 መሎጊያዎቹም በቀለበቶች ውስጥ ይግቡ መሠዊያውንም ስትሸከሙ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ወገኖች ይሁኑ።

7 And the staves shall be put into the rings, and the staves shall be upon the two sides of the altar, to bear it.

8 ከሳንቆች ሠርተህ ባዶ አድርገው በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ ያድርጉት።

8 Hollow with boards shalt thou make it: as it was shewed thee in the mount, so shall they make it.

9 የማደሪያውንም አደባባይ ሥራ በደቡብ ወገን የጥሩ በፍታ መጋረጆች ይሁኑለት፥ የአንዱም ወገን ርዝመት መቶ ክንድ ይሁን

9 And thou shalt make the court of the tabernacle: for the south side southward there shall be hangings for the court of fine twined linen of an hundred cubits long for one side:

10 ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሰሶችና ሀያ እግሮች ይሁኑለት የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ይሁኑ።

10 And the twenty pillars thereof and their twenty sockets shall be of brass; the hooks of the pillars and their fillets shall be of silver.

11 እንዲሁም በሰሜን ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሶሶች ሀያም እግሮች ይሁኑ ለምሰሶችም የብር ኩላቦችና ዘንጎች ይሁኑ።

11 And likewise for the north side in length there shall be hangings of an hundred cubits long, and his twenty pillars and their twenty sockets of brass; the hooks of the pillars and their fillets of silver.

12 በምዕራብም ወገን ለአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ አሥርም ምሰሶች፥ አሥርም እግሮች ይሁኑለት።

12 And for the breadth of the court on the west side shall be hangings of fifty cubits: their pillars ten, and their sockets ten.

13 በምሥራቅም ወገን የአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ይሁን።

13 And the breadth of the court on the east side eastward shall be fifty cubits.

14 በአንድ ወገን የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሁን ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ።

14 The hangings of one side of the gate shall be fifteen cubits: their pillars three, and their sockets three.

15 በሌላውም ወገን የመጋረጆች ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሆናል ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ።

15 And on the other side shall be hangings fifteen cubits: their pillars three, and their sockets three.

16 ለአደባባዩም ደጅ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ ሀያ ክንድ መጋረጃ ይሆናል ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ይሁኑ።

16 And for the gate of the court shall be an hanging of twenty cubits, of blue, and purple, and scarlet, and fine twined linen, wrought with needlework: and their pillars shall be four, and their sockets four.

17 በአደባባዩም ዙሪያ ላሉት ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች፥ የብርም ኩላቦች፥ የናስም እግሮች ይሁኑላቸው።

17 All the pillars round about the court shall be filleted with silver; their hooks shall be of silver, and their sockets of brass.

18 የአደባባዩ ርዝመት መቶ ክንድ ስፋቱም አምሳ ክንድ ይሁን፥ የመጋረጃውም ከፍታ አምስት ክንድ ይሁን መጋረጃውም ከጥሩ በፍታ፥ እግሮቹም ከናስ የተሠሩ ይሁኑ።

18 The length of the court shall be an hundred cubits, and the breadth fifty every where, and the height five cubits of fine twined linen, and their sockets of brass.

19 ለማገልገል ሁሉ የማደሪያው ዕቃ ሁሉ፥ ካስማዎቹም ሁሉ የአደባባዩም ካስማዎች ሁሉ፥ የናስ ይሁኑ።

19 All the vessels of the tabernacle in all the service thereof, and all the pins thereof, and all the pins of the court, shall be of brass.

20 አንተም መብራቱን ሁልጊዜ ያበሩት ዘንድ ለመብራት ተወቅጦ የተጠለለ ጥሩ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው።

20 And thou shalt command the children of Israel, that they bring thee pure oil olive beaten for the light, to cause the lamp to burn always.

21 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት ባለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲበራ ያሰናዱት በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን።

21 In the tabernacle of the congregation without the vail, which is before the testimony, Aaron and his sons shall order it from evening to morning before the Lord: it shall be a statute for ever unto their generations on the behalf of the children of Israel.