ኦሪት ዘፍጥረት Orit ZeFiTret
Genesis / Bereisheit #9
In Amharic and English

Can’t see Amharic font?

ኦሪት ዘፍጥረት 9

Genesis 9

1 እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው፦ ብዙ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት።

1 And God blessed Noah and his sons, and said unto them, Be fruitful, and multiply, and replenish the earth.

2 አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር አራዊት፥ በሰማይም ወፎች፥ በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱትም፥ በባሕር ዓሦችም ሁሉ ላይ ይሁን እነርሱም በእጃችሁ ተሰጥተዋል።

2 And the fear of you and the dread of you shall be upon every beast of the earth, and upon every fowl of the air, upon all that moveth upon the earth, and upon all the fishes of the sea; into your hand are they delivered.

3 ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ ሁሉን እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ።

3 Every moving thing that liveth shall be meat for you; even as the green herb have I given you all things.

4 ነገር ግን ነፍሱ ደሙ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ

4 But flesh with the life thereof, which is the blood thereof, shall ye not eat.

5 ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ ከሰውም እጅ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ።

5 And surely your blood of your lives will I require; at the hand of every beast will I require it, and at the hand of man; at the hand of every man’s brother will I require the life of man.

6 የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና።

6 Whoso sheddeth man’s blood, by man shall his blood be shed: for in the image of God made he man.

7 እናንተም ብዙ፥ ተባዙ በምድር ላይ ተዋለዱ፥ እርቡባትም።

7 And you, be ye fruitful, and multiply; bring forth abundantly in the earth, and multiply therein.

8 እግዚአብሔርም ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ።

8 And God spake unto Noah, and to his sons with him, saying,

9 እኔም እነሆ ቃል ኪዳኔን ከእናንተና በኋላ ከሚመጣው ከዘራችሁ ጋር አቆማለሁ

9 And I, behold, I establish my covenant with you, and with your seed after you;

10 ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፥ ከእናንተ ጋር ከመርከብ ለወጡት ለወፎች፥ ለእንስሳትም ለምድር አራዊትም ሁሉ፥ ለማንኛውም ለምድር አራዊት ሁሉ ይሆናል።

10 And with every living creature that is with you, of the fowl, of the cattle, and of every beast of the earth with you; from all that go out of the ark, to every beast of the earth.

11 ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።

11 And I will establish my covenant with you; neither shall all flesh be cut off any more by the waters of a flood; neither shall there any more be a flood to destroy the earth.

12 እግዚአብሔርም አለ፦ በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው

12 And God said, This is the token of the covenant which I make between me and you and every living creature that is with you, for perpetual generations:

13 ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል።

13 I do set my bow in the cloud, and it shall be for a token of a covenant between me and the earth.

14 በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች

14 And it shall come to pass, when I bring a cloud over the earth, that the bow shall be seen in the cloud:

15 በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።

15 And I will remember my covenant, which is between me and you and every living creature of all flesh; and the waters shall no more become a flood to destroy all flesh.

16 ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ።

16 And the bow shall be in the cloud; and I will look upon it, that I may remember the everlasting covenant between God and every living creature of all flesh that is upon the earth.

17 እግዚአብሔርም ኖኅን፦ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው።

17 And God said unto Noah, This is the token of the covenant, which I have established between me and all flesh that is upon the earth.

18 ከመርከብ የወጡት የኖኅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፥ ሴም፥ ካም፥ ያፌት ካምም የከነዓን አባት ነው።

18 And the sons of Noah, that went forth of the ark, were Shem, and Ham, and Japheth: and Ham is the father of Canaan.

19 የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው ከእነርሱም ምድር ሁሉ ተሞላች።

19 These are the three sons of Noah: and of them was the whole earth overspread.

20 ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ፥ ወይንም ተከለ።

20 And Noah began to be an husbandman, and he planted a vineyard:

21 ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ።

21 And he drank of the wine, and was drunken; and he was uncovered within his tent.

22 የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው።

22 And Ham, the father of Canaan, saw the nakedness of his father, and told his two brethren without.

23 ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም።

23 And Shem and Japheth took a garment, and laid it upon both their shoulders, and went backward, and covered the nakedness of their father; and their faces were backward, and they saw not their father’s nakedness.

24 ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ።

24 And Noah awoke from his wine, and knew what his younger son had done unto him.

25 እንዲህም አለ፦ ከነዓን ርጉም ይሁን ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።

25 And he said, Cursed be Canaan; a servant of servants shall he be unto his brethren.

26 እንዲህም አለ፦ የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።

26 And he said, Blessed be the Lord God of Shem; and Canaan shall be his servant.

27 እግዚአብሔርም ያፌትን ያስፋ፥ በሴምም ድንኳን ይደር ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።

27 God shall enlarge Japheth, and he shall dwell in the tents of Shem; and Canaan shall be his servant.

28 ኖኅም ከጥፋት ውኃ በኋላ ሦስት መቶ አምሳ ዓመት ኖረ።

28 And Noah lived after the flood three hundred and fifty years.

29 ኖኅም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ሆነ ሞተም።

29 And all the days of Noah were nine hundred and fifty years: and he died.