ኦሪት ዘጸአት Orit ZeTseAt
Exodus / Shemot #40
In Amharic and English

Can’t see Amharic font?

 

ኦሪት ዘጸአት 40

Exodus 40

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።

1 And the Lord spake unto Moses, saying,

2 ከመጀመሪያው ወር በፊተኛው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ።

2 On the first day of the first month shalt thou set up the tabernacle of the tent of the congregation.

3 በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ።

3 And thou shalt put therein the ark of the testimony, and cover the ark with the vail.

4 ገበታውንም አግብተህ በእርሱ ላይ የሚኖረውን ዕቃ ታሰናዳለህ መቅረዙንም አግብተህ ቀንዲሎቹን ትለኵሳለህ።

4 And thou shalt bring in the table, and set in order the things that are to be set in order upon it; and thou shalt bring in the candlestick, and light the lamps thereof.

5 ለዕጣንም የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ትጋርዳለህ።

5 And thou shalt set the altar of gold for the incense before the ark of the testimony, and put the hanging of the door to the tabernacle.

6 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት ታኖረዋለህ።

6 And thou shalt set the altar of the burnt offering before the door of the tabernacle of the tent of the congregation.

7 የመታጠቢያውን ሰንም በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑረህ ውኃ ትጨምርበታለህ።

7 And thou shalt set the laver between the tent of the congregation and the altar, and shalt put water therein.

8 በዙሪያውም አደባባዩን ትተክላለህ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ትዘረጋለህ።

8 And thou shalt set up the court round about, and hang up the hanging at the court gate.

9 የቅብዓቱንም ዘይት ወስደህ ማደሪያውን በእርሱም ያለውን ሁሉ ትቀባለህ፥ እርሱንም ዕቃውንም ሁሉ ትቀድሳለህ ቅዱስም ይሆናል።

9 And thou shalt take the anointing oil, and anoint the tabernacle, and all that is therein, and shalt hallow it, and all the vessels thereof: and it shall be holy.

10 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ ዕቃውንም ሁሉ ትቀባዋለህ፥ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል።

10 And thou shalt anoint the altar of the burnt offering, and all his vessels, and sanctify the altar: and it shall be an altar most holy.

11 የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀብተህ ትቀድሳለህ።

11 And thou shalt anoint the laver and his foot, and sanctify it.

12 አሮንንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አቅርበህ በውኃ ታጥባቸዋለህ።

12 And thou shalt bring Aaron and his sons unto the door of the tabernacle of the congregation, and wash them with water.

13 የተቀደሰውንም ልብስ አሮንን ታለብሰዋለህ በክህነትም ያገለግለኝ ዘንድ ቀብተህ ትቀድሰዋለህ።

13 And thou shalt put upon Aaron the holy garments, and anoint him, and sanctify him; that he may minister unto me in the priest’s office.

14 ልጆቹንም አቅርበህ ሸሚዞችን ታለብሳቸዋለህ

14 And thou shalt bring his sons, and clothe them with coats:

15 በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ መቀባታቸውም ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ክህነት ይሆንላቸዋል።

15 And thou shalt anoint them, as thou didst anoint their father, that they may minister unto me in the priest’s office: for their anointing shall surely be an everlasting priesthood throughout their generations.

16 ሙሴም እንዲሁ አደረገ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።

16 Thus did Moses: according to all that the Lord commanded him, so did he.

17 እንዲህም ሆነ በሁለተኛው ዓመት በፊተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ማደሪያው ተተከለ።

17 And it came to pass in the first month in the second year, on the first day of the month, that the tabernacle was reared up.

18 እግዚአብሔርም እንዳዘዘው ሙሴ ማደሪያውን ተከለ፥ እግሮቹንም አኖረ፥ ሳንቆቹንም አቆመ፥ መወርወሪያዎቹንም አደረገባቸው፥ ምሰሶቹንም አቆመ።

18 And Moses reared up the tabernacle, and fastened his sockets, and set up the boards thereof, and put in the bars thereof, and reared up his pillars.

19 ድንኳኑንም በማደሪያው ላይ ዘረጋ፥ የድንኳኑን መደረቢያ በላዩ አደረገበት።

19 And he spread abroad the tent over the tabernacle, and put the covering of the tent above upon it; as the Lord commanded Moses.

20 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ጽላቱን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረው፥ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ዘንድ አደረገ፥ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረው

20 And he took and put the testimony into the ark, and set the staves on the ark, and put the mercy seat above upon the ark:

21 ታቦቱን ወደ ማደሪያው አገባ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ አድርጎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ።

21 And he brought the ark into the tabernacle, and set up the vail of the covering, and covered the ark of the testimony; as the Lord commanded Moses.

22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ገበታውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ ከመጋረጃው ውጭ፥ በማደሪያው በሰሜን በኩል አኖረው

22 And he put the table in the tent of the congregation, upon the side of the tabernacle northward, without the vail.

23 እንጀራውን በላዩ በእግዚአብሔር ፊት አሰናዳ።

23 And he set the bread in order upon it before the Lord; as the Lord had commanded Moses.

24 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በገበታው ፊት ለፊት፥ በማደሪያው በደቡብ በኩል አኖረ

24 And he put the candlestick in the tent of the congregation, over against the table, on the side of the tabernacle southward.

25 ቀንዲሎቹን በእግዚአብሔር ፊት ለኰሰ።

25 And he lighted the lamps before the Lord; as the Lord commanded Moses.

26 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የወርቁን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በመጋረጃው ፊት አኖረ

26 And he put the golden altar in the tent of the congregation before the vail:

27 የጣፋጩን ሽቱ ዕጣን ዐጠነበት።

27 And he burnt sweet incense thereon; as the Lord commanded Moses.

28 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በማደሪያው ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ዘረጋ።

28 And he set up the hanging at the door of the tabernacle.

29 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት አኖረ፥ የሚቃጠለውንና የእህልን መሥዋዕት ሠዋበት።

29 And he put the altar of burnt offering by the door of the tabernacle of the tent of the congregation, and offered upon it the burnt offering and the meat offering; as the Lord commanded Moses.

30 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኖረ፥ ለመታጠቢያም ውኃን ጨመረበት።

30 And he set the laver between the tent of the congregation and the altar, and put water there, to wash withal.

31 በእርሱም ሙሴና አሮን ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ታጠቡ

31 And Moses and Aaron and his sons washed their hands and their feet thereat:

32 ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ወደ መሠዊያውም በቀረቡ ጊዜ ይታጠቡ ነበር።

32 When they went into the tent of the congregation, and when they came near unto the altar, they washed; as the Lord commanded Moses.

33 በማደሪያውና በመሠዊያውም ዙሪያ አደባባዩን ተከለ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ዘረጋ። እንዲሁም ሙሴ ሥራውን ፈጸመ።

33 And he reared up the court round about the tabernacle and the altar, and set up the hanging of the court gate. So Moses finished the work.

34 ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ከደነ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ።

34 Then a cloud covered the tent of the congregation, and the glory of the Lord filled the tabernacle.

35 ደመናውም በላዩ ስለ ነበረ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም።

35 And Moses was not able to enter into the tent of the congregation, because the cloud abode thereon, and the glory of the Lord filled the tabernacle.

36 ደመናውም ከማደሪያው በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በመንገዳቸው ሁሉ ይጓዙ ነበር።

36 And when the cloud was taken up from over the tabernacle, the children of Israel went onward in all their journeys:

37 ደመናው ባይነሣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር።

37 But if the cloud were not taken up, then they journeyed not till the day that it was taken up.

38 በመንገዳቸውም ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የእግዚአብሔር ደመና በማደሪያው ላይ በቀን ነበረና፥ እሳትም በሌሊት በዚያ ላይ ነበረና።

38 For the cloud of the Lord was upon the tabernacle by day, and fire was on it by night, in the sight of all the house of Israel, throughout all their journeys.