ኦሪት ዘዳግም Orit ZeDaGim
Deuteronomy / Devarim #33
In Amharic and English

Can’t see Amharic font?

ኦሪት ዘዳግም 33

Deuteronomy 33

1 የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት።

1 And this is the blessing, wherewith Moses the man of God blessed the children of Israel before his death.

2 እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥ በሴይርም ተገለጠ፤ ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥ ከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፤ በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው።

2 And he said, The Lord came from Sinai, and rose up from Seir unto them; he shined forth from mount Paran, and he came with ten thousands of saints: from his right hand went a fiery law for them.

3 ሕዝቡንም ወደዳቸው ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ናቸው፤ በእግሮችህም አጠገብ ተቀመጡ፤ ቃሎችህን ይቀበላሉ።

3 Yea, he loved the people; all his saints are in thy hand: and they sat down at thy feet; every one shall receive of thy words.

4 ሙሴ ለያዕቆብ ጉባኤ ርስት የሆነውን ሕግ አዘዘን።

4 Moses commanded us a law, even the inheritance of the congregation of Jacob.

5 የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ጋር በተከማቹ ጊዜ፥ ንጉሥ በይሹሩን ነበረ።

5 And he was king in Jeshurun, when the heads of the people and the tribes of Israel were gathered together.

6 ሮቤል በህይወት ይኑር፥ አይሙት ሰዎቹም በቍጥር ብዙ ይሁኑ።

6 Let Reuben live, and not die; and let not his men be few.

7 የይሁዳ በረከት ይህ ነውእንዲህም አለ፦ አቤቱ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥ ወደ ወገኖቹም አግባው፤ እጆቹ ይጠንክሩለት፤ በጠላቶቹ ላይ ረዳት ትሆነዋለህ።

7 And this is the blessing of Judah: and he said, Hear, Lord, the voice of Judah, and bring him unto his people: let his hands be sufficient for him; and be thou an help to him from his enemies.

8 ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፥ ቱሚምህና ኡሪምህ ለቅዱስህ ሰው ነው፥ በማሳህ ለፈተንኸው፥ በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፤

8 And of Levi he said, Let thy Thummim and thy Urim be with thy holy one, whom thou didst prove at Massah, and with whom thou didst strive at the waters of Meribah;

9 ስለ አባቱና ስለ እናቱ። አላየሁም ላለ፥ ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥ ልጆቹንም ላላወቀ፤ ቃልህን አደረጉ፥ ቃል ኪዳንህንም ጠበቁ።

9 Who said unto his father and to his mother, I have not seen him; neither did he acknowledge his brethren, nor knew his own children: for they have observed thy word, and kept thy covenant.

10 ፍርድህን ለያዕቆብ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በፊትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ይሠዋሉ።

10 They shall teach Jacob thy judgments, and Israel thy law: they shall put incense before thee, and whole burnt sacrifice upon thine altar.

11 አቤቱ፥ ሀብቱን ባርክ፥ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ የሚነሣበትን ወገብ ውጋው፥ የሚጠሉትም አይነሡ።

11 Bless, Lord, his substance, and accept the work of his hands: smite through the loins of them that rise against him, and of them that hate him, that they rise not again.

12 ስለ ብንያምም እንዲህ አለ፦ በእግዚአብሔር የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤ ቀኑን ሁሉ ይጋርደዋል፥ በትከሻውም መካከል ያድራል።

12 And of Benjamin he said, The beloved of the Lord shall dwell in safety by him; and the Lord shall cover him all the day long, and he shall dwell between his shoulders.

13 ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥ ምድሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረከ ይሁን፤ በሰማያት ገናንነት በጠል፥ በታችኛውም ቀላይ፥

13 And of Joseph he said, Blessed of the Lord be his land, for the precious things of heaven, for the dew, and for the deep that coucheth beneath,

14 በፀሐዩ ፍሬያት ገናንነት፥ በጨረቃውም መውጣት ገናንነት

14 And for the precious fruits brought forth by the sun, and for the precious things put forth by the moon,

15 በቀደሙትም ተራሮች ከፍተኛነት፥ በዘላለሙም ኮረብቶች ገናንነት፥

15 And for the chief things of the ancient mountains, and for the precious things of the lasting hills,

16 በምድሪቱም ገናንነትና ሞላዋ፥ በቍጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በተለየው ራስ አናት ላይ ይውረድ።

16 And for the precious things of the earth and fulness thereof, and for the good will of him that dwelt in the bush: let the blessing come upon the head of Joseph, and upon the top of the head of him that was separated from his brethren.

17 ለላሞች በኵር ግርማ ይሆናል ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፤ በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፤ የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥ የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።

17 His glory is like the firstling of his bullock, and his horns are like the horns of unicorns: with them he shall push the people together to the ends of the earth: and they are the ten thousands of Ephraim, and they are the thousands of Manasseh.

18 ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ፦ ዛብሎን ሆይ፥ በመውጣትህ፥ ይሳኮር ሆይ፥ በድንኳንህ ውስጥ ደስ ይበላችሁ።

18 And of Zebulun he said, Rejoice, Zebulun, in thy going out; and, Issachar, in thy tents.

19 የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ፥ የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፤ በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ።

19 They shall call the people unto the mountain; there they shall offer sacrifices of righteousness: for they shall suck of the abundance of the seas, and of treasures hid in the sand.

20 ስለ ጋድም እንዲህ አለ፦ ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፤ እንደ አንበሳይቱ ዐርፎአል፤ ክንድንና ራስን ይቀጠቅጣል።

20 And of Gad he said, Blessed be he that enlargeth Gad: he dwelleth as a lion, and teareth the arm with the crown of the head.

21 በዚያ የአለቃ እድል ፈንታ ቀርቶአልና የመጀመሪያውን ክፍል ለራሱ መረጠ፤ ወደ ሕዝብ አለቆችም መጣ፤ የእግዚአብሔርንም ጽድቅ፥ ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።

21 And he provided the first part for himself, because there, in a portion of the lawgiver, was he seated; and he came with the heads of the people, he executed the justice of the Lord, and his judgments with Israel.

22 ስለ ዳንም እንዲህ አለ፦ ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፤ ከባሳን ዘልሎ ይወጣል።

22 And of Dan he said, Dan is a lion’s whelp: he shall leap from Bashan.

23 ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ፦ ንፍታሌም በሞገስ ጠግቦአል፥ የእግዚአብሔርንም በረከት ተሞልቶአል፤ ባሕሩንና ደቡቡን ይወርሳል።

23 And of Naphtali he said, O Naphtali, satisfied with favour, and full with the blessing of the Lord: possess thou the west and the south.

24 ስለ አሴርም እንዲህ አለ፦ አሴር በልጆች የተባረከ ይሁን፤ በወንድሞቹ የተወደደ ይሁን፤ እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ።

24 And of Asher he said, Let Asher be blessed with children; let him be acceptable to his brethren, and let him dip his foot in oil.

25 ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል።

25 Thy shoes shall be iron and brass; and as thy days, so shall thy strength be.

26 ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም።

26 There is none like unto the God of Jeshurun, who rideth upon the heaven in thy help, and in his excellency on the sky.

27 መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ። አጥፋው ይላል።

27 The eternal God is thy refuge, and underneath are the everlasting arms: and he shall thrust out the enemy from before thee; and shall say, Destroy them.

28 እስራኤልም ተማምኖ፥ የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥ እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፤ ሰማያቱም ጠልን ያንጠባጥባሉ።

28 Israel then shall dwell in safety alone: the fountain of Jacob shall be upon a land of corn and wine; also his heavens shall drop down dew.

29 እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው? እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥ የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው። ጠላቶችህም ይገዙልሃል፤ አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።

29 Happy art thou, O Israel: who is like unto thee, O people saved by the Lord, the shield of thy help, and who is the sword of thy excellency! and thine enemies shall be found liars unto thee; and thou shalt tread upon their high places.